የስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ አስቸኳይ ጥሪ

ዜጎች በሀገራቸው በመረጡት ስፍራ በሰላም የመኖር እንዲሁም ንብረት የማፍራት እና ቤተሰብ መስርተው ልጆቻቸውን በተረጋጋ ሁኔታ የማሳደግ ሰብአዊ መብት እንዳላቸው በሀገሪቱ ህገ-መንግስት እና ሌሎች ኢትዮጲያ ባፀደቀቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች ውስጥ በግልፅ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ መንግስትም የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች የማክበር፣ የማስከበር እና የመጠበቅ ዋና ሃላፊነት እንዳለበት ይታወቃል፡፡ 

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን  የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የዜጎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ መሻሻል ይታይበታል የሚል ትልቅ ተስፋ የነበረ ቢሆንም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየተባባሰ እና እየከፋ መጥቷል፡፡ በተለይም የንፁሃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ በጅምላ መጨፍጨፍ እና ከመኖሪያቸው መፈናቀል የለት ተለት ዜና ከሆነ ሰነበተ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በነፃነት ከቦታ ቦታ መዘዋወር እና ሰርቶ ማደር እጂግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ የማያባራ እልቂት እና ሰቆቃ ዜጎች በሀገራቸው ባይተዋር እንዲሆኑ እና ደህንነት እንዳይሰማቸው እያደረገም ይገኛል፡፡ ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በዚሁ ጉዳይ ላይ በተለያዩ ጊዜያት መግለጫዎችን ሲያዎጣ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ የመብት ጥሰቱ የቀጠለ በመሆኑ ዛሬም የሚመለከታቸው ሁሉ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ እና ጥሰቱን እንዲያስቆሙ መወትወቱን ቀጥሏል፡፡

ድርጅታችን በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተለይም በወለጋ የተለያዩ ወረዳዎች በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል፤ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና ሊገታ ያልቻለው የዜጎች ስቃይ እጅጉን አሳስቦታል፡፡ ይህ ሊገታ ያልቻለ የጅምላ ግድያ ሂደት ተባብሶ በጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም በቄለም ወለጋ ዞን በጊዳሚ ወረዳ ንፁሃን ሰዎች በጅምላ መገደላቸውን መንግስት ገልጧል፡፡ የዞኑ አስተዳደር ዜጎቹ የተገደሉት በኦሮሞ ነፃነት ጦር መሆኑን ገልፆ 87 ንፁሃን ዜጎች በጅምላ ተገድለው አስክሬናቸው በአንድ ቦታ እና 81 ተጨማሪ ሰዎች በተለያዩ ቦታ በድምሩ 168 ንፁሃን ተጨፍጭፈው መገኘታቸውን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በጥር 02 ቀን 2014 የአማሮ ልዩ ወረዳ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉ/ፅ/ቤት ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የታጠቁ ሀይሎች ከዲላ ወደ አማሮ በመጓዝ ላይ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ በሰነዘሩት ጥቃት 3 ሰዎች መገደላቸውን፣ አራት ሰዎች  መቁሰላቸውን እና ንብረቶች መዘረፋቸውን ገልጸዋል። የወረዳው የመንግስት አካላት በአካባቢው እንደዚህ አይነት ጥቃቶች እጅግ በተደጋጋሚ ጊዜ መፈፀማቸውን በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን እና በአስር ሽዎች መፈናቀላቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ጥቃቶች እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዲሁም የችግሩን ተደጋጋሚነትና አሳሳቢነት የሚያሳዩ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ ታጣቂዎች በሚፈፅሙት ጥቃት በኦሮሚያ ክልል በኩል ጎሐፅዮን፣ በአባይ በረሃ እና ሌሎች አካባቢዎች ወደ አማራ ክልል በሚገቡ አሽከርካሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ግድያ፣ ድብደባና እገታ እየደረሰ መሆኑን አሽከርካሪዎች ገልፀዋል፡፡ በአካባቢው በአንድ ዓመት ብቻ 10 አሽከርካሪዎች መገደላቸውን ዶይቸ ቬለ በየካቲት 07 ቀን 2014 ዘግቧል፡፡ ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በአሽከርካሪዎች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች እና መሰል ችግሮች የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ የመስራት እና በህይወት የመኖር መብቶችን የሚገድቡ በመሆናቸው መንግስት አስቸኳይ እና ተገቢ እርምጃዎችን በመውሰድ የዜጎችን ደህንነት እና ህይወት የመጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣ ያሳስባል፡፡

ስለሆነም ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ መንግስት እየተፈፀሙ ያሉ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማቆም የሚከተሉትን የመፍትሄ እርምጃዎች እንድወስድ ጥሪውን ያቀርባል፡-

  • የቅድመ  መከላከል ተግባር እንዲያከናውን፣ ተጠያቂነትን እንድያሰፍን እና ዜጎችን ከተደጋጋሚ ጥቃት ነፃ ለመሆናቸው ዋስትና እንዲሰጥ፤
  • ለተጎጂዎች ተገቢውን እገዛ እና ድጋፍ እንዲያደርግ እና ዘላቂ መፍትሄን እንዲያረጋግጥ፤

በተጨማሪም ድርጅታችን ይህ ጉዳይ እልባት ያገኝ ዘንድ ከመንግስት በተጨማሪ የሲቪል ማህበረሰብ እና ብዙሃን መገናኛ ድርጅቶች፣ በአካባቢው የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች እና እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን ዘግናኛና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት  መቋጫ ያገኝ ዘንድ ውትወታ እንዲያደርጉ፣ እንዲቃወሙ እና እንዲያወግዙ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *