ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በሃገራችን በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት በማድረግ እየተፈፀሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አስከፊ ደረጃ እየደረሰ መሆኑን ድርጅታችን በተደጋጋሚ ባወጣቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ገልጿል። አያይዞም ስጋቱን  በመንግስትና ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት በኩል ምን እርምጃ መወሰድ እንዳለበት በተደጋጋሚ ሲያሳስብ እንዲሁም ምክረ ሃሳቦችን ሲሰጥም ቆይቷል።

ዜጎች መብታቸው እና ነፃነታቸው ተረጋግጦ የመኖር ህጋዊ እና ተፈጥሮአዊ መብት እንዳላቸው እሙን ነው፡፡ ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የሚሰነዘሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም እጅግ አስከፊ እና ተደጋጋሚ የሆኑ  ጭፍጨፋ እና እልቂቶች ስር እየሰደዱ  ይገኛሉ፡፡

ከየካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም  ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ጃርቴ  ወረዳ ደቢስ ቀበሌ በርካታ ንጹሃን ዜጎች በግፍ እና በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ፣ አካል ማጉደል ፣ የንብረት ዘረፋ እና መፈናቀል  እንደተፈፀመባቸው እንደ ቪኦኤ ባሉ እና ሌሎች ሚድያዎች መሰረት መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ በተመሳሳይ በዚሁ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ በሶስት የዞኑ አካባቢዎች ላይ በመጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም መጠነ ሰፊ የሆነ እና ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ በአማራ ተወላጆች ላይ መድረሱ በተለያዩ ሚዲያዎች ማለትም በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ፣ አዲስ ስታንዳርድ እና በሌሎችም ተዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል ተደጋጋሚ የዜጎች እልቂት እየተስተናገደበት ባለው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል እና ካማሼ ዞን ከመጋቢት 22 እና 23 ቀን 2013 ዓም ጀምሮ በንጹሃን ዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ የጥቃት እርምጃዎች ተፈጽመዋል። ድርጊቶቹም የበርካቶች ሕይወት የቀጠፉ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጥቃቱን ፈርተው የተሰደዱ እና በጥቃቱ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው።ባለፉት ጥቂት ቀናትም ይህ ድርጊት መቀጠሉን  እና ዜጎችም ለተደጋጋሚ ጥቃት መጋለጣቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ቀርበው ስጋታቸውን እና አቤቱታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። ይህን መሰል በማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች መደጋገም እና ዛሬም ንጹሃን ዜጎች ስጋት ውስጥ ሆነው መንግስት እና ሌሎች አካላት እንዲታደጓቸው ጥሪ እያቀረቡ መሆኑ ድርጅታችንንም በጥልቅ አሳስቦታል፡፡

ይህ ማንነትን መሰረት ያደረገ እልቂት በተመሳሳይ በአማራ ክልል አጣዬ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ኬሚሴ፣ ማጀቴ እና አካባቢው ላይ ባሉ ወረዳዎች ተከስቶ በንጹሃን ዜጎች ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት አድርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በመጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት በእነዚህ አካባቢዎች  በደረሰ ጥቃት 104 ሰዎች መገደላቸውን እና ሶስት ቤተክርስቲያኖች፤ አንድ ትምህርት ቤት መቃጠላቸውን እንዲሁም ከመቶ በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን አመላክቷል፡፡ በተጨማሪም በአንቡላንስ ለህክምና በመወሰድ ላይ የነበሩ ቁስለኞች ከአንቡላስ እንዲወርዱ ተደርገው ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ተገድለዋል፡፡

በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ከመጋቢት 24 ቀን 2013 ዓም ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት እስከ 100 የሚደርሱ ሰዎች ህይወት ማለፉን እና የንብረት ውድመት መድረሱን እንደ ዶይቸ ቬለን ያሉ የተለያዩ ሚድያዎች የተገለፀ ሲሆን ለዚህም ከፍተኛ የዜጎች ህይወት መጥፋት እንደምክንያት የተነሳው የድንበር ጉዳይ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

በሀገሪቱ የሚከሰቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አድማሳቸውን እያሰፉ እና እየተባባሱ መምጣታቸውን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ይገኛሉ፡፡

ላለፉት ሁለት አመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተከታታይ በሆነ መልኩ በዜጎች ህይወት ላይ ያነጣጠሩ የጅምላ ጭፍጨፋዎች መከሰቱ የአገሪቱን የሰብአዊ መብት አያያዝ ወደ ከፋ ደረጃ አድርሶታል። ዜጎች ለህይወታቸውም ሆነ ላፈሩት ንብረት ደህንነት ዋስትና ሊሰጣቸው የሚችለው መንግስት እንደሆነ ይታወቃል። ይሁንና በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ የመንግስት አካላት እነዚህን አደጋዎች ቀድሞ ለመከላከልም ሆነ ድርጊቶቹ ከፍተኛ ጉዳት ሳያስከትሉ በፊት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተመጣጣኝ እና ሕጋዊ እርምጃዎችን ባፋጣኝ ሲወስዱ አይሰተዋሉም። ይህ አይነቱ በመንግሥት አካላት በኩል የሚስተዋለው ከልክ ያለፈ ቸልተኝነት ወይም ኃላፊነትን በአግባቡ ያለመወጣት ችግር የአገሪቱን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ወደከፋ ደረጃ ላይ ያደረሰው መሆኑን በርካታ ጥናቶች እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች መግለጫዎች ያመላክታሉ።

በአገራችን እየከፋ የመጣው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና በንጹሐን ዜጎች ላይ ያነጣጠሩና በየዕለቱ የሚፈጸሙ እጅግ ሰቅጣጭ የጅምላ ግድያዎች እና መፈናቀሎች ከሌሎች የፖለቲካ ቅራኔዎች ጋር ተደማምረው አገሪቱን ወዳልተረጋጋ የግጭት ቀጠና እየቀየሯት ይመስላል።  በተለይም በኦሮሚያ ክልል ወለጋ፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል እና ካማሸ ዞን እንዲሁም በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን እና በሰሜን ሸዋ አዋሳኝ አካባቢዎች ክቡር የሆኑ የሰው ልጆች በየቀኑ የሚገደሉበት እና ለተዳጋጋሚ ጥቃት የሚጋለጡበት በሰዎች ላይ አስከፊ እና ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚፈፀሙባቸው፣ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎችቤትና ቀያቸውን ለቀው ለመፈናቀል የሚገደዱበት አካባቢዎች መሆን ከጀመሩ ሰነባብተዋል::

 ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ ወራት ባወጣቸው ተመሳሳይ መግለጫዎቹ መንግስት እነዚህን መሰል ጥቃቶችን እና ግጭቶችን እንዲያስቆም እና ምን የመፍትሔ እርምጃዎችን ቢከተል የተሻለ እንደሚሆን ጭምር ስንጠቁም እና ደጋግመንም ስንወተውት ቆይተናል። ይሁንና ችግሮቹ ተገቢውን ያህል ትኩረት ሊያገኙ ባለመቻላቸው አድማሳቸውን እያሰፉ እና የተጎጂውን ማህበረሰብ ቁጥር እየጨመረ፤ እንዲሁም የጥቃቱ አይነት እና የጭካኔውም ደረጃ እየከፋ መምጣቱን በቅርብ ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱ የመብት ጥሰቶች ከበቂ በላይ አስረጂዎች ናቸው።

እንደ ድርጅታችን እምነት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲቀንሱ፣ እንዲቆሙ እና እንዲሻሻሉ ከሚረዱት ስልቶች አንዱ በመብት ጥሰት ፈጻሚነት የተሳተፉ አጥፊዎችን እና ተባባሪዎቻቸውን በሕግ አግባብ ተጠያቂ ማድረግ ሲቻል ነው። በመንግስት የተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ የሚገኙ አካላት ላይ በቂ ምርመራ ተወስዶ አጥፊዎች ተጠያቂ የሚሆኑበት ግልጽ እና ፍትሃዊ አሠራር አለመዳበሩ ጥፋት አጥፍቶ ያለመጠየቅ ባህልን ከማጎልበትም አልፎ ዜጎች በፍትህ እጦት እንዲሰቃዩም ምክንያት ይሆናል። ተጠያቂነትን ባለማስፈን ምክንያት እየተበራከተ የሄደው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ድርጅታችንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ተቋማችን መንግስት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ሰብአዊ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበር እና የማዳበር ግዴታዎቹን በአግባቡ መወጣት የሚያስችለውን ስልት እንዲቀይስ እና ተጠያቂነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ማስገንዘብ ይወዳል፡፡

ስለሆነም ተቋማችን መንግስት የሚከተሉትን የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲወስድ ጥሪውን ያቀርባል፡-

  • ከመቼውም ጊዜ በላይ በቂ ትኩረት በመስጠት እየተከሰቱ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በአፋጣኝ እንዲያስቆም፣ የቅድመ መከላከል ስራዎችን እንዲሰራ እና የዜጎችንም ህይወት መታደግን ቅድሚያ እንዲሰጥ፤
  • በተደጋጋሚ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተከሰተባቸው ባሉት አካባቢዎች አስፈላጊውን ህዝባዊ እና ተቋማዊ መፍትሄዎችን እንዲወስድ፤
  • ዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሰላም የመኖር፣ የመስራት እና ንብረት የማፍራት መብታቸውን እንዲያረጋግጥ እና ለዜጎች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ፤
  • በሰዎች ላይ አስከፊ የሰብአዊ ጥሰት እየፈፀሙ ባሉ ግልሰቦችና ቡድኖች እንዲሁም በተባባሪዎቻቸው ላይ ሕጋዊ  እና  ለድርጊቶቹ ተምጣጣኝየሆነ  እርምጃ እንዲወስድ
  • አስከፊ የሆነው ሀገራዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ጉዟችን ይቆም ዘንድ ሃገራዊ የውይይት እና የምክክር መድረኮችን እንዲፈጥር፤

ከቀያቸው ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ እና ከትትል እንዲያደርግእናሳስባለን

ድርጅታችን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እንዲሻሻል ችግሮችን በአግባቡ አጥንቶ ለመንግስት ጥቆማና ምክረ ሃሳቦችን ከመስጠት ጀምሮ  ዜጎች መብቶቻቸው እና ግዴታዎቻቸውን አውቀው የራሳቸውን መብት እንዲያስከብሩ እና የሌሎችንም ሰዎች መብት እንዲያከብሩ በማስተማር የበኩሉን ጥረት ያደርጋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *