ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የዜጎችን ማንነት መሰረት አድርገው የሚፈፀሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ሲያሳስብ ቆይቶል፡፡ ነገር ግን ይህ ድርጊት አድማሱን በማስፋት እና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ተጠናክሮ በመቀጠል የዜጎች በህይዎት የመኖር መብት፣ ንብረት የማፍራት እና ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም የመኖር እና ሌሎች መሰረታዊ መብቶቻቸው ከመቸውም ጊዜ በላይ አደጋ ላይ እንዲወድቁ እያደረገ ይገኛል፡፡

ምንም እንኳን እነዚህን ድርጊቶች መንግስት እያወገዘና ጥቃቶቹን በቁጥጥር ስር ለማድረግ እየሞከረ መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለፀ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ ያላቸውን አካላት በአግባቡ በመለየት እና በተሳትፎቸው ልክ በህግ አግባብ ተጠያቄ ማድረግ ላይ በሚገባው ልክ ሃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም፡፡

በተለይም በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ማለትም በኦሮሚያ ክልል አክቲቪስት እና የሚድያ ባለቤት የነበሩት አቶ ጀዋር መሃመድ መንግስት ለጥበቃ የመደባቸውን የጥበቃ ሃይሎች ተከበብኩ በሚል በማህበራዊ ድህረገፅ ያስተላለፉትን የድረሱልኝ ጥሪ ተከትሎ፣ የኦሮምኛ ሙዚቃ ድምፃዊና የመብት ተሞጋች አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ፣በዚሁ ክልል በተደጋጋሚ በታጠቁ አካላት በሚደርስ ጥቃት፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በተደጋጋሚ ዘርንና ማንነትን መሰረት ባደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች፣ በደቡብ ክልል ማንነትን መሰረት ባደረጉ ግጭቶችና ጥቃቶች፣ በትግራይ ክልል ማይካድራ በሚባል ቦታ ማንነትን መሰረት ያደረገ እጅግ አሰቃቂ ጥቃት፣ በሱማሌና አፋር አዋሳኝ አካባቢዎች በደረሱ ግጭቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል፣ መቁሰል፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም እየተከሰተ ያለ ቢሆንም በዚህ ልክ በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖችና የመንግስት አካላት ባላቸው ተሳትፎ መጠን በህግ ተጠያቂ ሲሆኑ አይታይም፡፡ ከዚህ ባለፈም በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ከአንድ ጥቃት የተረፉ ዜጎች ለሌላ ተመሳሳይ ጥቃት እየተጋለጡ መሆኑን ለማየት ተችሏል፡፡  በዚህ ምክንያትም ተጎጂዎችም ሆኑ መላው ህብረተሰብ በዚህ የጥፋት ተግባር ተሳታፊዎች ላይ ህጋዊና አስተማሪ  እርምጃ አለመወሰዱና ተጠያቂነት አለመስፈኑ በሀገሪቱ እየተደጋጋመ ለሚከሰተው ዘርንና ማንነትን መሰረት ላደረገው ጥቃት እንደ አባባሽ ምክንያት ሲጠቅሱት ይስተዋላል፡፡

ከክልሎች መንግስታትና ከፌደራል መንግሰት ባሻገርም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች (ሴቶች እና ህፃናትን ጨምሮ) በአንዳነድ የሀገሪቱ ስፍራዎች እጅግ በሚሰቀጥጥ አኳኋን ማንነትን መሰረት ባደረገ ጥቃት ሲገደሉ፣ ሲቆስሉ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲደርስባቸው ብሎም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ሲፈናቀሉ ለጉዳዩ ትርጉም በሚሰጥ ደረጃ ትኩረት መስጠት አልቻለም፡፡ ይህም ድርጊቱ በተደጋጋሚ እንዲፈፀም አስተዋፅዖ ከማድረጉም በላይ  አጥቂዎቹ ወደህግ ለማቅረብም ሆነ ድርጊቱን ለማቆም የሚደረገው ጥረት እጅግ አናሳ እዲሆን ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ጥቃቶች ባሻገር በታህሳስ 13 2013 ከለሊቱ 10፡00 አካባቢ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ቡለን ወረዳ ቡክጂ ቀበሌ ማናንነትን መሰረት ባደረገ ጥቃት ከ220 በላይ ዜጎች መሞታቸውን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ባልደረቦች ለተለያዩ የሚዲያ አካላት ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው ክትትል አገኘሁት ባለው መረጃ የሟቾችን ቁጥር 207 መሆኑን በመግለጫው አመላክቶል፡፡ በሌላ በኩል በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞን ውስጥ ከ ህዳር 1-11 2013 ድረስ በነበረ ግጭት 66 ሰዎች መገደላቸውን በታህሳስ 16፣ 2013 ኢሰመኮ ባደረገው ጥናት ገልፆል፡፡

በመሆኑም ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች  በኢትዮጵያ፤ ለክልል መንግስታት፣ የፌደራል  መንግስትና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የመፍትሔ  እርምጃዎች እንዲወስዱ ጥሪውን ያቀርባል፡-

  • የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መንግስታት በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች   ዜጎችን በማንነታቸውን መሰረት  ጥቃት እንዲፈፀም ያደረጉ እና በተለያየ ደረጃ ተሳትፎ ያላቸውን መንግስታዊ ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በተሳትፎቸው ልክ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ፤
  • አለምአቀፉ ማህበረሰብ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በተለይም በአሁኑ ወቅት በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በንፁሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ትርጉም ባለው ደረጀ ትኩረት መሰጠት አለመቻሉ ጉዳዩ የበለጠ እንዲባባስ አድረጎል፡፡ ስለሆነም ይህንን በሰው ልጅ ስብዕና ላይ እየተፈፀመ ያለን የወንጀል ድርጊት  በአንድነት  እንዲያወግዝ እና በጥፋቱ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ያለበትን ሀላፊነት እንዲወጣ፤
  • የብሄር ማንነትን መሰረት አድረገው የሚደርሱ ጥቃቶች ለዜጎች የህይወት ማጣት፣ መፈናቀል እና ንብረት መውደም መንስኤ በመሆኑ መንግስት ከሚመለካታቸው አካላት ጋር በመሆን እየደረሰ ያለውን ተደጋጋሚ ጥቃት ፖለቲካዊ እና ህጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያስቆም ይገባዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *