ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በህዳር ወር በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ የተስተዋሉ ዋና ዋና ክስተቶችን መሰረት በማድረግ ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶል፡፡

ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በሀገሪቱ በተደጋጋሚ የዜጎችን ማንነት መሰረት አድርገው እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች የተበራከቱ መሆኑ የሚያሳስብው ሲሆን በተለይም፡-

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ለዓመታት በዘለቀው ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት የበርካታ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ደግሞ ለጉዳት መዳረጋቸውን ከተለያዩ አካላት የሚወጡ ሪፖርቶችን መሰረት በማድረግ ለማወቅ ተችሏል።

በህዳር ወር 2013 አመተ ምህርት በተደጋጋሚ በደረሱ ዘርን መሰረት ያደረጉ ጥቃት ምክንያት  በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉና የቆሰሉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከቡለን ወደ ቻግኒ በርካታ ሰዎችን ጭኖ ይጓዝ በነበረ የህዝብ ትራንሰፖርት ተሽከርካሪ ላይ ቂዶ በምትባል ሰፈር በደረሰ ጥቃት በርካታ የሚሆኑ ዜጎች ጥቃት የደርሶባቸውና አብዛኞቹም መሞታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ጥቃት አሰቃቂና ፍፁም ኢሰብዓዊ  በሆኑ ድርጊቶች የታጀቡ መሆናቸውን ተጎጂ ግለሰቦችና የአይን እማኞች  ሁኔታውን ለተለያዩ የሚዲያ አካላት ገልፀዋል፡፡

ምንም እንኳን በአካባቢው የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማስቆም የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስን ያካተተ ኮማንድ ፖስት በስፍራው ከተቋቋመ ወራት የተቆጠረ ቢሆንም  በአካባቢው ባሉ ነዋሪዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ ነው።

በተለያዩ የመተከል ዞን ቀበሌዎች ማለትም በጫንጮ ቀበሌ፣በዳሊቲ ቀበሌ፣ አልባሳ ቀበሌ፣ ገዲሳ ቀበሌ፣ ሙዘን ቀበሌ፣ አልባሳ ቀበሌ፣ ገደሬ ቀበሌ ለበርካታ ሳምንታት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ተፈናቃዮቹ ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይም በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ ባለው የኦነግ ሽኔ ታጣቂ ቡድን በሚያደርገው ጥቃት ምክንያት በርካቶች ህይወታቸውን ማጣታቸውን እንዲሁም ንብረታቸው እንዲወድም የተደረገባቸው መሆኑን ለመገናኛ ብዙሃን ጣቢያዎች ተጎጂዎችና የአይን እማኞች አሳውቀዋል፡፡ ምንምእንኳን የፊደራል መንግስትና የኦሮሚያ ክልል በታጣቂ ቡድኑ ላይ ተከታታይ የሆነ እርምጃ እየወሰደ መሆኑንን ቢገልፅም በታጣቂ ቡድኖች በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶቹ ግን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡   

በሌላ በኩል የፌደራል መንግስቱ ህግ የማስከበር ዘመቻ ብሎ በጠራው እንቅስቃሴ ምንም እንኳን የመቀሌ ከተማን ጨምሮ ሁሉንም የትግራይ ከተሞች ከህውሃት ሀይሎች እጅ እንዲወጡ ያደረገና የተቆጣጠረ ቢሆንም በ ጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው መሰረተ ልማቶች በመኖራቸው ምክንያት በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከእርዳታ ሰጪ ቡድኖች የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በመሆኑም ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች  በኢትዮጵያ፤ የፌደራል  መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት  ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የመፍትሔ  እርምጃዎች እንዲወስዱ ጥሪውን ያቀርባል፡-

  • የብሄር ማንነትን መሰረት አድረገው የሚደርሱ ጥቃቶች ለዜጎች የህይወት ማጣት መንስኤ በመሆኑ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል፡፡ በተለይም በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ መንግስት ሊያሰቆም ይገባዋል፡፡
  • በተለይም ጉዳዩ የሰዎችን ዘር መሰረት ያደረገ ጥቃት መሆኑንን ከግንዛቤ በመውሰድ የአለም አቀፉ ማህበረሰብም በኢትዮጵያ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ውስጥ እየደረሰ ስላለው ፍፁም ኢሰብአዊና አሰቃቂ የሰው ልጅ ጥቃት ትኩረት እንዲሰጡት እናሳስባለን፡፡
  • በታጣቂ ቡድኖች በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የፌደራል መንግስትና የክልል መንግስታት እንዲያስቆሙ፣ በዚህ ጥቃት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡ ለተፈናቀሉ ወገኖችም ድጋፍ እንዲደረግ እናሳስባልን፡፡
  • የፌደራል መንግስቱ ህግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በነበሩ ግጭቶች ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው መሰረተ ልማቶች በመኖራቸው ምክንያት በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር እያስከተለ በመሆኑ ለነዚህ ችግሮች አስቸኳይ የሆኑ የመሰረተ ልማት ጥገናዎችን ማድረግ፤ እንዲሁም ከእርዳታ ሰጪ አካላት ጋር በመተባበር የአስቸኳይ ግዜ ድጋፍ ለሚያሰፈልጋቸው ዜጎች አገልግሎት የሚሆኑ ቁሣቁሶችን በጦርነቱ ለተጎዱ ነዋሪዎች በአፋጣኝ ማድረስ ይኖርበታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *