ጋዜጣዊ መግለጫ

ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በነሐሴ ወር በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ የተስተዋሉ ዋና ዋና ክስተቶችን መሰረት በማድረግ ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶል፡፡ ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ 

በደቡብ ብ/ብ/ህ/ ክልላዊ መንግስት የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በነበረው ግጭት የንፁኃን ህይወት ማለፉን በመንግስት አካላት፤ እንዲሁም በተለያዩ የመብት ተሟጋች ቡድኖች ተገልፆል፡፡ አንዳንዶችም የፀጥታ ኃይሉ ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ በመውሰዱ ምክንያት ለብዙዎች ሞት እና ለብዙዎች አካል መጉደል መንስኤ ሊሆን እንደቻለ ዘግበዋል፡፡  

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ለተቃውሞ በተጠሩ ሰልፎች ለመሳተፍ ወደ አደባባይ በወጡ ግለሰቦች እና በፀጥታ ሀይሎች መካከል በተከሰተው ግጭት ምክንያት የሰዎች ህይወት መጥፋቱ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ ነሐሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም  የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ የፀጥታ ሀይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ጥሪውን አቅርቦል፡፡ 

የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማጥናት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረገው ጥረት የሚያበረታታ ቢሆንም እሰከአሁን ድረስ ሙሉ ሪፖርት ግን አልቀረበም፡፡ ነሐሴ 8 ቀን /2012 ዓ/ም የወጣው የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ መግለጫ እንደሚያመለክተው አሁንም ቢሆን ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች የጥቃቱ ኢላማ የሆኑ ዜጎች አሁንም የጥቃት ስጋት ያለባቸው መሆኑን ከነዋሪዎቹ ያገኘውን መረጃ መነሻ በማድረግ ስጋቱን ገልጿል ፡፡

ከዚህ ባሻገርም ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጾ ታሳሪዎቹ በሚገኙባቸው አንዳንድ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ  እስር ቤቶች ውስጥ  አሳሳቢ የሆኑ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግሮች መስተዋላቸውን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡ 

በሀገሪቱ የኮቪድ 19 መከሰት ተከትሎ የወጣው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የህዘብን መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች፤ በተለይም የመሰብሰብ ነጻነትን  በከፋ ሁኔታ የሚገድብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የአዋጁ አተገባበር ወጥነት የጎደለው በመሆኑ የተነሳ በተለያዩ አካላት ቅሬታዎች እየቀረቡ መሆኑን ታዝበናል፡፡ በተለይም በመንግስት አካለት የሚጠሩ እና የሚዘጋጁ ስብሰባዎች ያለ ምንም እንቅፋት  ቁጥሩ ብዙ የሆነ ህዝብ እየተሳተፈ በመካሄድ ላይ ሲሆኑ በተቃራኒው ደግሞ ሌሎች አካለት በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተጠሩ የጋዜጣዊ መግለጫ እና ስብሰባዎች አጥጋቢ ያልሆኑ ምክንያቶች እየተሰጡ በጸጥታ ኃይሎች እንዲስተጓጎሉ መደረጉን እና በመንግስት በኩል የተወሰደው እርምጃም ተገቢ አለመሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች  በኢትዮጵያ፤ መንግስት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የመፍትሔ  እርምጃዎች እንዲወስድ ጥሪ ያቀርባል፡-

  • የክልል እና የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ያላቸውን ሚና እና የዜጎችን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በቅጡ በመረዳት  በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን በሚገልጹ ወይም የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ዜጎች ላይ  የፀጥታ ኃይሎች ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ እንዳይወስድ መንግስት ተገቢውን ክትትልና ጥንቃቄ እንዲያደርግ፤ እንዲሁም በጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃዎች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ እና ያልተመጣጠነ ኃይል በሚጠቀሙ የፀጥታ አካላት ላይ ተገቢ እርምት መውሰድ ይኖርበታል፡፡የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግስታት በተወሰዱ የኃይል እርምጃዎች እና በደረሱት ጉዳቶች ላይ በቂ እና አፋጣኝ ምርመራ በማካሄድ የምርመራቸውን ውጤት እና የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎችን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርጉ፣
  • የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያን ተከትሎ ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች  ለዳግም ጥቃት ስጋት ያለባቸው ነዋሪዎችን መንግስት ተገቢ ጥበቃ እንዲደረግላቸው፣ እንዲሁም የጥቃት ማስፈራሪያ እና ዛቻዎችን በሚያደርሱ ቡድኖች ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ አርምጃ እንዲወስድ፣
  • በኦሮሚያ ከተከሰተው የሰላም መደፍረስ ችግር ስፋት አንፃር የእስር ሁኔታን በሚመለከት የመንግስት አቅም ውስንነት እንዳለ ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች  በኢትዮጵያ የሚገነዘብ ቢሆንም በቁጥጥር ስር የሚውሉ ሰዎች የአያያዝና ሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ ችላ ሊባል አይገባም፡፡ በመሆኑም መንግስት በተቻለ አቅምና ፍጥነት እነዚህን ችግሮች እንዲፈታ፣
  • የኮቪድ 19 መከሰት ተከትሎ የወጣው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አፈፃፀም  ያለ ምንም አድሏዊ አሰራር በመንግስት አካለትም ሆነ በሌሎች አካላት መካከል፤ በተለይም በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ማህበራት ላይ በእኩልነት ተፈጻሚ እንዲሆን እና የዜጎችን መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ እንዲተገበር እናሳስባለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *