ጋዜጣዊ መግለጫ

ሐምሌ 26፣ 2012 ዓ.ም

የኢትዮጵያ መንግስት ገለልተኛ የሆኑ ባለሙያወችን እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ያካተተ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን በማቋቋም ከአድሎ የፀዳ ምርመራ ሊያካሂድ ይገባል። 

የጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ መንግስት በተለያዩ ዘርፎች ማሻሻያዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል አፋኝ የሆኑ ህጎችን በማሻሻል የፖለቲካ እና የሲቪክ ምህዳሩን ማስፋት በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ ይህም ግለሰቦች እና ድርጅቶች ሃሳባቸውን በነፃነት በማራመድ ለሰብአዊ መብቶች መከበርና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፤ እንዲሁም ለሀገር እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽዎ እንዲያበረክቱ እድል ፈጥሯል፡፡ በሌላ በኩል መንግስት የሕግ የበላይነትን በማስፈን እና የዜጎችን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ የሆነ ቸልተኝነት አሳይቷል፡፡  በመሆኑም በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ብሄርን እና ሀይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸው አልፏል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የሕዝብ እና የአገር ሃብት እና ንብረት ወድሟል፤ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከሚኖሩበት ቀያቸው ተፈናቅለው ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል፡፡    

በመንግስት ባለሥልጣናት ተደጋግሞ በመገናኛ ብዙሃን እንደተገለጸው በያዝነው አመት ጥቅምት ወር የለውጥ አቀንቃኝ እና የሚድያ ባለቤት የሆኑት አቶ ጀዋር መሃመድ መንግስት ለጥበቃ የመደበለላቸውን የጥበቃ ሃይሎች ሊያነሳብኝ ነው፣ በታጠቁ ቡድኖች ተከብቤአለሁ በሚል ለደጋፊዎቻቸው ያስተላለፉትን የድረሱልኝ ጥሪ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል 97 ንጹሃን ዜጎች ሲገደሉ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይሁንእና መንግስት የተፈጠረውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በአግባቡ በማጣራት ጥሰት ፈጻሚዎቹን ለፍርድ በማቅረብ እና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ፤ እንዲሁም በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች  አስፈላጊው ካሳ እንዲከፈላቸው እና ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ሲገባው ነገሩን አለባብሶ ማለፉ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም መንግስት ህግ የማስከበር ግዴታውን በወቅቱ እና በአግባቡ ባለመወጣቱ፤ እንዲሁም  አስተማሪ የሆነ እርምጃ ባለመወሰዱ በዚሁ ክልልም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው እና የከፋ የሰብአዊ መብት ቀውስና ጥሰት ያስከተሉ ክስተቶች በሰፊው እንዲፈፀሙ ምክንያት ሆኗል፡፡ 

በተጨማሪም ይህንኑ መንግስት ላይ እየታየ ያለውን ህግን የማስከበር እና አስፈላጊውን ቁጥጥር የማድረግ ክፍተት በመጠቀም አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ጥላቻን ሲሰብኩ እና ብሔርን እና ኃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በንፁሃን ዜጎች ላይ እንዲፈፀም ሲያነሳሱ ከርመዋል፡፡ በቅርቡም በሰኔ 22/2012 ዓ.ም. የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ እና የመብት ተሞጋች የሆነው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እና በአዲስ አበባ በተከታታይ ቀናት በተከሰተው ሁከት በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል።  በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየቤተ እምነቱ ለመጠለል ተገደዋል። በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚገመት የሀገር ሀብት እና የግለሰቦች ቤት እና ንብረት በእሳት ወድሟል። በአዲስ አበባም አስራ አራት ሰዎች መገደላቸውና ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት መውደሙ ይታወቃል፡፡ 

የአይን እማኞች፣ የጥቃቱ ሰለባዎች እና ሌሎች የተለያዩ የመረጃ ምንጮች እንደሚያረጋግጡት ጥቃቱ ያነጣጠረው በክልሉ ውስጥ በሚኖሩ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የሌላ ብሄር ተወላጆች እና የክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ የነበረ መሆኑን ነው። ድርጊቱም የተፈፀመውም ጽንፍ በያዙ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች እንደሆነ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ አብዛኞቹ ጥቃት ፈፃሚዎች ድርጊቱን ከጀርባ ሆነው በሚያቀናብሩ አካላት ተደግፈው እና  የመጓጓዣ አገልግሎትም  ተመቻችቶላቸው እንደነበር እና ጥቃቶቹ ከተፈፀሙባቸው አካባቢዎች ውጪ ካሉ ሥፍራዎች የመጡ ወጣቶች መሆኑን እማኞች መስክረዋል። ጥቃቱን ያደረሱትም ግለሰቦች በደንብ የተደራጁ፣ ቀድሞ በተጠና እና ዝግጅት በተደረገበት  መልኩ ይንቀሳቀሱ እንደነበር ከአካባቢው የተገኙ መረጃዎች ያረጋግጣሉ።  በአንዳንድ ሥፍራዎች እነዚሁ ቡድኖች ኢላማ ያደረጉዋቸውን ሰዎች የስም ዝርዝር ቀድመው በመያዝ እና ከቤት ቤት እየተንቀሳቀሱ ጥቃት ይፈጽሙ እንደነበርም  መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ እነዚህ አጥፊዎች የሌላ ብሄር ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችን ብቻ ሳይሆን የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችንም ጭምር የጥቃት ኢላማ በማድረግ ግድያና ንብረት ማውደም መፈጸማቸውን ማረጋገጥ ተችሏል። በተወሰኑ አካባቢዎች የእስልምና ተከታይ የሆኑ የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ ዜጎች ንብረትም ወድሟል። ሙሉ ለሙሉ ከወደሙት እና ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ንብረቶች እና መሰረተ ልማቶች መካከልም ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ትላልቅ የንግድ ተቋማት፣ ፋብሪካዎች፣ ሆቴሎች እና በርከት ያሉ የመኖሪያ ቤቶች ይገኙበታል፡፡  

በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃት አድራሾቹ  የጥቃት ሰለባ ያደረጎቸውን ግለሰቦች አካል በመቆራረጥ እና እጅግ አሰቃቂ በሆነ መልኩ አሰቃይተው በመግደል፤ እንዲሁም የሟቾቹን አስክሬን መንገድ ለመንገድ በመጎተት ከሰው ልጅ ስብእና በወጣ መልኩ በድል አድራጊነት ስሜት ሲጨፍሩ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው እና መግቢያ ያጡ፤ እንዲሁም ስጋት ያደረባቸው በሺዎች የሚገመቱ ዜጎች በተለያዩ የእምነት ተቋማት ውስጥ እና ሌሎች ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሚያጋልጥ መልኩ ተፋፍገው እንደሚገኙም ይታወቃል፡፡  

ይህ ሁሉ እልቂት እና የሃብት ውድመት ሲደርስ መንግስት አስፈላጊውን የመከላከል እና ጥቃቱን በአፋጣኝ የማስቆም እርምጃ መውሰድ ባለመቻሉ የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት በመጠበቅ እረገድ በአገሪቱ ሕገ መንግስት እና በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች የተጣሉበትን ግዴታዎች ሳይወጣ ቀርቷል፡፡ የመንግስት የመገናኛ አውታሮችን ጨምሮ በተለያዩ ምንጮች እንደተገለፀው ግጭቶቹ በተከሰቱበት በአብዛኞቹ አካባቢዎች የሚገኙ የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች እና የአካባቢዎቹ መንግስታዊ መዋቅሮች ዝምታን መርጠዋል። በተለይም የፀጥታ አካላት የተቋቋሙበትን አላማ በመዘንጋት እና ከበላይ ትዕዛዝ አልተሰጠንም በሚል ተቀባይነት የሌለው ሰንካላ ምክንያት አደጋውን የማስቆም እና ጥቃቱን የመከላከል እርምጃ በአፋጣኝ ሳይወስዱ ቀርተዋል፡፡ ብሎም በአንዳንድ ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የፀጥታ አካላት መሳሪያቸውን ለጥቃት ፈፃሚዎቹ እስከመስጠት ድረስ የደረሰ እገዛ እና ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር በክልሉ ባለስልጣናት ተገልጧል፡፡ ይህም አገር አማን ነው ብለው እና ለደህንነታቸው ጥበቃ የሚያደርግላቸው መንግስት መኖሩን አምነው በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች እና የክርስትና እምነት ተከታዮች በክልሉ የመንግስት መዋቅር ላይ አመኔታ እንዲያጡ እና የደህንነት ስጋትም እንዲሰማቸው አድርጓል፡፡ 

በአሁኑ ወቅትም መንግስት የአካባቢውን ሰላም እና ፀጥታ እንደሚያስከብር፤ እንዲሁም ለተጎጂዎች ፍትህን እንደሚያረጋገጥ ቃል በመግባት እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎችንም፤ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ገልጧል፡፡ ይሁንና ከላይ እንደተገለፀው አንዳንድ በክልሉ መንግስት በተለያየ ደረጃ ያሉ አመራሮች የጥቃቱ ደጋፊ እና እንዲሁም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ በመሆናቸው ጉዳዩ ከወገንተኝነት በፀዳ እና ገለልተኛ በሆነ አካል ሊጣራ እና መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተጨማሪም በሀገሪቱ ፅንፍ የወጣ ብሄርተኝነት እና የሀይማኖት አክራሪነት ስር እየሰደደ እንደመምጣቱ እና ጥቃቱ ብሔር እና ኃይማኖት ተኮር እንደመሆኑ ትክክለኛ ፍትህን ለማስፈን እና ለችግሩ በማያዳግም ሁኔታ መፍትሄ ለማበጀት ይረዳ ዘንድ የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ እና ለሀገር አንድነት የሚጠቅም መፍትሄ የሚያስቀምጥ ገለልተኛ አካል ተዋቅሮ ጉዳዩን እንዲመረምር፣ መረጃዎችን እንዲያሰባስብ እና በምርምር ላይ የተመሰረተ የውሳኔ ሃሳብም እንዲያቀር ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ 

በመሆኑም ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች  በኢትዮያ፤ መንግስት እና የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የመፍትሔ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥሪ ያቀርባል፡፡ 

ለኢትዮጵያ መንግስት 

  • ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ የእምነት ተቋማት እና መጠለያዎች ተጠልለው ለኮቪድ-19 በሚያጋልጥ ሁኔታ ለሚገኙ ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ እና እርዳታ እንዲያደርግ፤ መልሰው የሚቋቋሙበትንም ሁኔታ እንዲያመቻች፣
  • ገለልተኛ የሆኑ ባለሙያወችን እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ያካተተ ገለልተኛ ቡድን በማቋቋም ከአድሎ የፀዳ ምርመራ እንዲያካሂድ፣ 
  • እየተካሄዱ የሚገኙ ምርመራዎች እና የማጣራ ሥራዎች በህግ አግባብ እየተከናወኑ መሆኑን እንዲያረጋግጥ እና በህግ ጥላ ስር የዋሉትንም ተጠርጣሪዎች በህጉ መሰረት ለፍርድ እንዲያቀርብ፣  
  • በህግ አግባብ ምዝገባ ሳያከናውኑ የሚንቀሳቀሱ እና አላማቸውም ጥላቻን መስበክ፣ ፅንፈኝነትን እና ግጭቶችን ማባበስ የሆኑ የሲቪል ማህበራት እና የፖለቲካ ድርጅቶች ነቅሶ በማውጣት፤ እንዲሁም የገንዘብ ምንጮቻቸውን በመለየት ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣
  • በህዝቦች መካከል መቃቃርን የሚፈጥሩ እና ለግጭት የሚጋብዙ የጥላቻ ንግግሮችን እና መልዕክቶችን  የሚያስተላልፉ  መገናኛ ብዙሃንእና ማህበራዊ ድህረ ገፆች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣ 
  • በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ገብተው ሳለ አሁንም ታጥቀው የሚገኙ እና በተለያዩ ጊዜያት ጥቃቶችን እየፈፀሙ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የተደራጁ ቡድኖች ትጥቅ እንዲያስፈታ፣ 
  • የክልል እና የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ህግን በማስከበር ረገድ ያለቸውን ሚና እና የተጣለባቸውን ኃላፊነት  የሚያትት መመሪያ እንዲያወጣ፣
  • ለተጎጂዎች እውነተኛ ፍትህን እንዲያሰፍን፣ አስፈላጊውን ካሳ እንዲከፍል እና በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት በማያወላዳ ሁኔታ እንዲያስከብር፣
  • የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንዲከላከል፣ ጥሰቶች ተፈፅመው ሲገኝ ደግሞ በአግባቡ እና በወቅቱ እንዲያጣራ እንዲሁም በፈፃሚዎች ላይ በህግ አግባብ አስተማሪ የሆኑ እርምቶችን እንዲወስድ እናሳስባለን። 

ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች 

  • የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውን ብሔርን እና ኃይማኖትን መሰረት ያደረገ እና በመቶዎች ለሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ህልፈት፣ በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ለሚገመት ንብረት ውድመት እና ከአስር ሺዎች በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነውን ጥቃት በገለልተኛ አካል እንዲጣራ እንዲያደርግ እና በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት እንዲስጠብቅ ግፊት እንዲያደርጉ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡ 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *